.. Ethiopian Cult Information Center (ECIC)በክርስቶስ ስም የመጡብን ቁጭ በሉዎች (ነፃነት ዘለቀ) Fake pastors in Ethiopia

By ነፃነት ዘለቀ


የት ተኝተህ ከረምክ እንዳልባል እንጂ በሁሉም ረገድ ሀገራችን ሊገመት ከሚችለው በላይ መሞቷን ዛሬ ነው የተረዳሁት፡፡ አንድ ሕዝብና አንድ ሀገር እንዲህ የተስተካከለ ውድቀት ላይ (ሁለንተናዊ ገጽታ ያለው ውድቀት) ሲደርስ በዓለም ታሪክ ይህ የመጀመሪያው መሆን አለበት፡፡ ምናልባትም ለአንድ ሕዝብ ከላይም ይሁን ከታች የሚላከው መንግሥትና የመንግሥት አመራር አባላት ከሕዝብ አጠቃላይ ኑባሬያዊ ይዘት አኳያ ተለክተው የሚሰፉ እንደሆኑ የሚነገረው ልክ ሣይሆን አይቀርም፡፡ መጽሐፉም “እግዚአብሔር ክፉን ሕዝብ መቅጣት ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥ ያነግሣል” ይላል፡፡ ብሂላችንም “አላህ ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” ብሎ የመጽሐፉን ቃል ያጸናዋል፤ “ያልዘሩት አይበቅልም” መባሉም ከዚህ ገሃድ የወጣ የክሽፈት እውነታ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እስከዚህን ወርዶ መፈጥፈጡን ስመለከት ቴዴ አፍሮን የመሰሉ ልዑላን ባይኖሩ ኖሮ በተስፋ መቁረጥ መንፈስ አንዲት ገመድ ይዤ ወደሚቀርበኝ ዛፍ በሮጥኩ ነበር – እንዲህም ስል ደግሞ ስመጥርነት ሊያስከትል ከሚችለው የልብ ዕብጠትና በትዕቢት ሠረገላ የመንሣፈፍ አጓጉል ጠባይ ልዑላንና ልዕልታት ልጆቻችንን ጌታ እንዲጠብቅልንና የኔ ዓይነቱን ገመድ አንጠልጣይም ልብ እንዲሰጥልን በመለመን ጭምር ነው – ሆ! ክፉ ምኞትን መፈጸም እኮ እኮ ከባድ አይደለም፡፡ እንዴ፣ እዚህ ብታዩ የሚጫወትብን እኮ በዛ! ብሎ ብሎ የሠፈር ዱርዬ በየአጥቢያችን የሃይማኖት ኪዮስክ እየከፈተና በቁስላችን እንጨት እየሰደደ ይቀልድብን? አዳሜ ከዱርዬው መንግሥት ጋር እየተሻረከ በሞባይላችን በየደቂቃው የሚልከው አጭር መልእክት መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቶናል፡፡ ሎተሪ በሎተሪ ሆነናል – ለማንም ሲደርስ ደግሞ አይታይም፡፡ ብሔራዊ ሎተሪም ራሱ አምስት ሣንቲም ላይሰጥ ቂሉን ዜጋ ይቦጠቡጠዋል፡፡ ድሃ ተስፈኛ ነውና ለሎተሪ ቀልባችን ስስ መሆኑን ገምተው በሞባይልም በወረቀትም በአልኮልና ለስላሳ መጠጥም ሁሉም ብልጣብልጥ የወያኔ አጋፋሪና አዘጥዛጭ ይቺን ሎተሪ እያዞረ ይበዘብዘናል፡፡ ወይ መዓልቲ! ለአጥንታችን እኮ አስቆሩን፡፡ የትግሬ ዘመን ግዴላችሁም አዲስ የሆድ ሪከርድ ሳያስመዘግብ ቦታውን አይለቅም፡፡ ማን ይሆን እኒህን የተራቡ የቀን ጅቦች ጃዝ ብሎ የለቀቀብን ጃል!

ዛሬ ጧት ለዘመድ ጥየቃ በሄድኩበት ቤት የርቀት መቆጣጠሪያውን ይዤ ወደ ቲቪው የተገናኘውን ሪሲቨር ከፍ ዝቅ እያደረግሁ ቻናሎችን እፈትሽ ገባሁ፡፡ አይቻቸው የማላውቃቸው ብዙ የሃይማኖት ጣቢዎችን አየሁ፡፡ የሀገር ውስጥም የውጭ ሀገራትም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስም ለምን ይቅርብኝ በሚል ይመስላል ጣቢያ ከፍቷል – ሃይማኖቱም ጠፍቶ ሃይማኖተኛውም ከመለኮታዊ ቃልና የእምነት መንገድ ወጥቶ ለሥጋው አድሮ በሚገኝበት የድብብቆሽ ሁኔታ ጣቢያው እንዲኖር ተደርጓል – ሃቅ ተሸፍና እውነት እየተረመረመች፣ ጳጳሱ ለዘሩ አድልቶ ቤተ አምልኮቱን በማይማን ወያኔዎች እየሞላና ድንቁርና እንደፀጋ ተቆጥሮ ገንዘብ በሚመለክባት ቤተክርስቲያን ምን ሊሰበኩን ይህን ጣቢያ እንደከፈቱ ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት እውነተኛ ሃይማኖተኛ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ነፍስና ሥጋ ተጣልተው መንፈስ ቅዱስ በሸሻት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተደረገ ያለውን ልዘርዝር ብል ወረቀትም ጊዜም ብዕርም አላገኝም፡፡ ባጭሩ የመጥፋት ምሣሌ ሆነናል፡፡ የሀሰት ትምህርት በማር ተለውሶ የሚሠራጭ የመሆኑ መሠረታዊ እውነት በታሳቢነት ተይዞልኝ ከየሱሳውያኑ ጣቢያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ምራቅ የዋጠን ሰው ሣይቀር ሊስቡ የሚችሉ አቀራረቦች ታዝቤያለሁ፡፡ ብዙዎቹ ግን የቁጭ በሉነታቸው እጅግ የወረደ ደረጃ እንኳንስ ትልቅን ሰው ማሕጸን ውስጥ ያለን የስድስትና የሰባት ወር ሽል ማታለል አይችሉም፡፡ ይህ ዓይነቱ በፖለቲካው የለመድነው ቁጭ በሉ በሃይማኖቱ ገብቶ በጌታችን በመድሓኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲከሰት ማየት በርግጥም የትንቢቱን ፍጻሜና የኢየሱስን ዳግመኛ ምፅዓት አፍ አውጥቶ በግልጽ የሚናገር ነው – ላስተዋለ፡፡ በጣም የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ነን፡፡ የፖለቲካው ቁጭ በሉ ሣያንሰን የመረገማችን መጠን ለከት አጣና በሃይማኖቱም እንደሕጻን ይጫወቱብን ገቡ፡፡ በዚህን መሰሉ ስብከትና የፈውስ ፕሮግራም የሚታለል ዜጋ ይዘህ እንዴት ብለህ ሀገርን ያህል ትልቅ ጉዳይ መገንባት እንደሚቻል እግዜር ይወቅ፡፡ ሕዝብ ሳይገነባስ ሀገር ምንድን ነው? በጩልሌ በቀላሉ የሚታለል ወገን ይዘህ መድረሻህ የት ነው? “ገና ሳስበው ደከመኝ” ያለው ማን ነበር? ብዙዎቻችን ያለንበት የንቃተ ኅሊና ደረጃ እጅግ ያስደነግጣል፡፡ ወያኔዎች ከተሳካላቸው ዘመቻዎች አንዱና ዋናው ሕዝብን በዕውቀትና ግንዛቤ ማጫጫትና እንደነዱሽ ማድረግ መሆኑን ለመገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ግባ፡፡ ሆድ ነግሦ ጭንቅላት አንሶ ስታይ ዕድልህን ረግመህ በመጣህበት እግርህ በፍጥነት ትመለሳለህ፡፡ ዘረኝነት፣ ስካር፣ ዝሙት፣ ሙስና፣ ልመና፣ራስ ወዳድነት፣ ፍርደ-ገምድልነት፣ ማይምነት፣ ሆዳምነት፣ ይሉኝታ-ቢስነት፣ ሀፍረተ-ቢስነት፣ ሶዶማዊነት፣ ስግብግብነት፣ መተት፣ ወዘተ. እላያችን ላይ ተቆልለውብን አፍነው ሊገድሉን የቀራቸው ጊዜ ግፋ ቢል ግማሽ ሐሙስ ቢሆን ነው፡፡ ፎቅና አስፋልት ሊደብቁት ያልቻሉትን ማኅበረሰብኣዊ ገመናችንን ሳት እያላቸው ኢቲቪን መሰል የወያኔ ሚዲያዎችና ዛሬ የተመለከትኳቸው የሃይማኖቱ ዘርፍ ጩልሌ የቲቪ መስኮቶች አውጥተው እየዘረገፉት ነው፡፡ እናንተም እዩዋቸውና የት እንደደረስን ታዘቡ፡፡ መርዶ ነጋሪ አትበሉኝ – አልቆልናል፡፡

አንዱ ጣቢያ ላይ እንዲህ አየሁ፡፡ የክርስቶስን ቦታ በጉልበት ነጥቆ በፈዋሽነት ቦታ ላይ የተቀመጠው ማንትስ የሚባል ፓስተር ቀድመው የተዘጋጁ “የመዳን ምሥክሮች”ን ከሴትም ከወንድም እያስቀረበ ያስለፈልፋል፡፡ እነዚያ “የዳኑ” ሰዎችም ሆድ መጥፎ ነውና ለሚያገኙዋት ትንሽ ሣንቲም ሲሉ በሉ የተባሉትን ይላሉ (እነዚህ ሰዎች በአንድ ቀደም ያለ ወቅት አንድ በረንዳ አዳሪ በገንዘብ ገዝተው ‹እኚህ ጳጳስ ኦርቶዶክስን ክደው ኢየሱስን ተቀበሉ› ብለው ከወያኔ የማይተናነስ ድራማ ማስተላለፋቸውንና ቀሲስ ዘበነ የተባለ ካህን ማጋለጡን ለምናስታውስ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ቅሌታሞችና የሰይጣን ፈረሶች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡)… ወያኔም እንዲህን ዓይነት ድሆች ለስብሰባና ለሠልፍ እየጠራ ከድሃዋ እናታችን ባዶ ካዝና እየመዘበረ በውሎ አበል ስም ይከፍላል፡፡ እነዚህ በፓስተር እገሌ “ያመኑና የተጠመቁ” ምሥኪን ሆድ አደሮች እንዲህ በማለት አላንዳች ሀፍረት “ሲመሰክሩ” ሰማሁ – “ አንተን በቲቪ እስክሪን ስዳስስ የነቀርሣ በሽታዬ ውልቅ ብሎ ሲሄድ ታየኝ፤ ከዚያን ጊዜ በኋላ ጌታን ተቀበልኩ”፡፡ ኃያሉ አምላክ እግዚአብሔር ይፍረድ፡፡ መፍረዱስ አይቀርም – እኔ ግን በጣም ቸኮልኩ፡፡ እንዲህ የሚጫወቱበትን ዱርዬዎች እስከዚህ መታገሱ ለምን እንደሆነ አልገባህ አለኝ፡፡ ለነገሩ ያኔም ሲሰቀል ምራቃቸውን ሲተፉበትና ሲያላግጡበት፣ የእሾህ አክሊል ሲደፉበትና ቀሚሱ ላይ ዕጣ ሲጣጣሉበት፣ በመጨረሻም ከወንበዴዎች ጋር ልክ እንደወንጀለኛ ሲሰቅሉት ለነሱው አዘነ እንጂ አንድም እርምጃ አልወሰደባቸውም፡፡ የነዚያ እርጉማን አጋንንት ልጆች ናቸው አሁንም በየሽርንቁላው ትናንሽ ቤቶችን እየተከራዩና ድንኳን እየተከሉ በስሙ ሊከብሩ ሀገር ምድሩን ሞልተውት የሚገኙት፡፡ ቀናቸው በመድረሱ አሁን እጅግ በመቅበዝበዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ ወያኔና እነዚህ ጉዶች ሀፍረት የሚባል አልፈጠረባቸውም፡፡ ሁለቱም የሰይጣን ልጆች ናቸውና መጨረሻቸውም አንድ ነው፡፡ ወደሌላው አመራሁ፡፡ ናትናኤል ሞላልኝ የሚባል ፓስተር ተብዬ በግርጌው የተጻፈበት ቁጭ በሉ ጣቢያ ላይ ደረስኩ፡፡ በየትኛውም የዕድሜ ዘመኔ አፍሬ የማላውቀውን ያህል አፈርኩ፡፡ ወያኔ ጥሩ ጥሩ ምትኮቹን በሃይማኖቱ ዘርፍም እንደተካ ተረዳሁ፡፡ አንድ ዱርዬ ፓስተር ሕዝቡን በሀሽሽ መሰል ስብከት አይሉት ጥንቆላ ያማልለው ይዟል፡፡ አስቀድሞ ላዘጋጃት አንዲት ቆንጆ እንዲህ ይላል “ክርስቶስ እያሳየኝ ነው፤ ክፍልሽ ዱባይ ነው፡፡ እዚያ ነው ያለው ያንቺ እንጀራ፡፡ 17 ሺህ ዱርሃም ነው የሚከፈልሽ፡፡ ሚያዝያ 11 ሂጂ፤ ሃሌ ሉያ! ሻንታራራም — ፑንቶራሩማማሙ — ሾንተር ቮንገር ሃማማሮራራሮታ… አንቺ ብቻ አይደለሽም፡፡ ወንድምሽም እዚያ ይሄዳል፡፡…”(እንዲህ “ተሠርቶ” እንጀራ ይበላል፤ ይበሉን! ሲያንሱን ነው!) እግዚአብሔር ያሳያችሁ፡፡ ወዴት እየሄድን ነው? ታምራት ገለታ ዞሮ ዞሮ በየት በኩል መጣብን? ተራ የመንደር ማጅራት መች እንዴት ብሎና በየትኛው የትምህርትና የብቃት ደረጃው ነው የሃይማኖት ሰባኪና ፈዋሽ የሚሆነው? እነዚህ ሰዎች ታሪካቸው ቢፈተሸ እርግጠኛ ነኝ መነሻቸው ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ነው – እዚያ ያዳበሩትን የወሬቋትነት በመነሻ ወረትነት ይዘው በሰይጣን መንፈስ በመነዳት ሕዝብን ያተራምሳሉ – በነሱው አገላለጽ ‹ጌታ ይገስጻቸው›፡፡ … የተሰበሰበው ሰው እንደዛር ይደልቃል፤ ያጎራል – አንዳንዱ ለሥልት ሆን ተብሎ የተዘጋጀ አጫፋሪ ነው፤ አንዳንዱ ግን በየዋህነት የመጣና የጨነቀው ነው፡፡ ያ ድለቃና ጭብጨባ ሙቀት የሰጠው ዱርዬው ፓስተር ቀንድና ጭራ በሌለው የጥንቆላ መሰል ንግግሩ እየታጀበ ከወዲያ ወዲህ በኩራት ይመላለሳል – አለባበሱ፣ የፀጉሩ አቆራረጥ – አነጋገሩ – ፍጹም ዱርዬ ስለሚያስብለው ከዱርዬ ያነሰ ስም ልሰጠው አልቻልኩም፡፡ ከዕውቀት ዕውቀት፣ ከችሎታ ችሎታ የለውም፡፡ ተራ ዱርዬ – በቃ፡፡ ማታ የት ሊገኝ እንደሚችል ከግምት ባለፈ ማወቅ ይቻላል፡፡

ከነዚህ ፓስተሮች የተረዳሁት አንድ ነገር አለ፡፡ ምናልባትም ከአንድ በላይ፡፡ አንደኛ የጊዜውን መድረስ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ተገንዝቤያለሁ – እነሱም ያውቃሉ፤ ምክንያቱም የትንቢቱን ቃል ሳይወዱ በባሕርይ አባታቸው በሰይጣን ተገድደው እየፈጸሙ እንደሆነ ትንሹ እግዚአብሔር – ማለትም ኅሊናቸው – ቢያንስ ማታ ማታ ሲተኙ አይነግራቸውም ብዬ አላምንም፡፡ ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ መንፈስ ተሞላን ብለው ይቀዣብሩ እንጂ አንድም የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ የላቸውም፡፡ ሊኖራቸው ከቻለ ሊኖራቸው የሚችለው – ከቅጥፈታቸው በተጨማሪ – የሰይጣን መንፈስ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ከሰማይ እሳት እስከማዝነብ የሚደርስ ሥልጣን ምድር ላይ አለው፡፡ መጽሐፉ “ብዔል ዘቡል በብዔል ዘቡል አይወጣም” ቢልም ይህ አባባል ጥያቄን እንደሚያጭር በየመናፍቃን “አብያተ ክርስቲያናት” ባደረግሁት የግል ጥናትና ተሞክሮ ያረጋገጥኩት ነገር አንዱ ርኩስ መንፈስ በሰው ውስጥ ሸማቂ ሌላው ርኩስ መንፈስ በፓስተሩ(ረዳቱ) በኩል አስወጪ በመሆን የዋሃንን ማታለል እንደሚችሉ ነው፡፡ ዝርዝሩ ሰፊ ነውና አልገባበትም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዓለምን እያሽከረከራት የሚገኘው እርሱ ነው – ሣጥናኤል፡፡ መገለጫው የተለያዬ ይሁን እንጂ የዓለም የወቅቱ ገዢ እርሱ ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም፡፡ ከሆሊውድ እስከ ቦሊውድ፣ ከዋይት ሀውስ እስከ አራት ኪሎ የምንሊክ ቤተ መንግሥት፣ ከፔንታጎን እስከ ቢሾፍቱ የቆሪጥ የሐይቅ ውስጥ ጽ/ቤት ድረስ የመሸገው ግልጽ ሰብዓዊና ሥውር አጋንንታዊ ኃይል ሁሉ የመጨረሻውን ፊሽካ የሚጠባበቅ የዓለማችን መጥፊያ አርማጌዴዎናዊ መሣሪያ ነው፡፡ በርትቶ መጸለይ ነው ጎበዝ! መዘናጋት የለም፡፡ በነዚህ ዱርዬዎች ግን እባካችሁን አንጃጃል፡፡ ይህን ጉድ እያየሁ ወያኔን መታገል ለኔ ቀልድ መስሎ ታየኝ፡፡ አገር ምድሩን እያበከቱት የሚገኙት ሰይጣናት ሃይ ካልተባሉ – አይበልብንና – ሀገራዊና ሕዝባዊ ሞታችን እውን ሆኖ በቅርብ ሥርዓተ ቀብራችን መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ወያኔ ለዚህ እንደዳረገን እማኝ የማያሻው እውነት ነው፡፡ በታላላቅ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች በተለይም በኦርቶዶክሱ በሰገሰጋቸው ከፓትርያርክ እስከተራ ዲያቆን በሚደርስ ሥልጣንና ክህነተ ማዕረግ ያሉ ደናቁርት የአጋንንት ውላጅ ወያኔዎች ያማረሩት ሕዝብ መጠጊያ ሲያጣ ወደባሰው የሰይጣን ጎራ በመሸሽ ሊደበቅ ይሞክራል፡፡ እዚያም የሚጠብቀው የከፋ ነገር ነውና ያበደው አብዶ ሌላው መሀል ሜዳ ተንሣፍፎ ይቀራል፡፡ በመካከሉ ሕዝብ ይጠፋል፡፡ በሞራል፣ በሃይማኖትና በባህል የጠፋ ሕዝብ ደግሞ ለማንኛውም ወጀብ የተጋለጠ ነው፡፡ እግዚኦ በሉ ታዲያ፤ እግዚኦ እንበል፡፡ ጊዜው የእግዚኦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እግዚኦታ ቢከለከልም በውጭ ያላችሁ እግዚኦ በሉልን፡፡ እኛ ጸሎትም ተመጥኖ ነው የሚሰጠን፣ የፈለግነውን አንጸልይም፡፡ ጸሎት ብቻም ሳይሆን ዘፈንም ተለክቶ ነው የሚሰጠንና የምናዳምጥ፤ ለአብነት ቴዲን እንዳናዳምጥ ብዙ ጫና አለብን፡፡ ለዚህስ ሳይሆን ይቀራል በተለይ ማታ ማታ አዲስ አበባ ውስጥ ጆሮ የሚያደነቁር ትግርኛ ዘፈን የሚከፈተው? ያ ፍቁድ ነው – ሳትገደድም አትቀርም፡፡ መኪና ውስጥ ትግርኛ ከፍተህ ሆስፒታሉንና ትምህርት ቤቱን ሁሉ እያደነቆርክ ብትሄድ ምናልባች ትሸለማለህ እንጂ አትወቀስም፡፡ ሌላ ልክፈት ብትል ግን መኪናህም በትምክህተኝነትና በጠባብነት ትታሰርና የዝገት ሲሳይ ሆና ልትቀር ትችላለች፡፡ ወይ ኢትዮጵያ! ምን ዓይነት ዳፍንታም ኢትዮጵያ ሆነች እባካችሁን፡፡ ሌላው ይቅር ማሰብም ተለክቶ ነው የሚሰጠን እኮ፡፡ ምን ማሰብ እንዳለብን ወሳኙ ወያኔ ነው፡፡ እንደልቤ አስባለሁ ብትል ወያኔ አንቀጽ ጠቅሶ ከርቸሌ ያወርድሃል ወይንም “በመንገድ ሊያመልጥ ሲል ተገደለ” ሊልህና ያለፍርድ ድራሽህን ሊያጠፋው ይችላል፡፡ የግላዲያተር ዘመን ተመልሶ መጣና በእኛ ስቃይና ሞት የሚደሰት ወያኔ ትግሬ ታዘዘብን፡፡ ሰው አላወቀልንም እንጂ ከእንስሳት በታች እየኖርን ነው — እናም እግዚኦታም ሲያንሰን ነውና ጸልዩልን፡፡ ቀኑ የእግዚኦታና የኤሎሄ ነው፡፡ ለስንብት ልድገመው – ወይ መዓልቲ!

nzeleke35@gmail.com “ኤሎሄ አሌሄ ላማሰበቅታኒ”፡፡ አባት ሆይ ለምን ተውከን? እስከዚህንስ ለምን ጨከንክብን? ምሕረትህ የት አል? ለነዳዊትና ሰሎሞን የገለጥክላቸው ቸርነትህስ አሁን ወዴት አለ? “እንደኃጢኣታችን ሣይሆን እንደምሕረትህ ብዛት ማረን” እያልን እንጸልይ የለምን?…

We Welcome Your comments, compliments, and complaints! Send Us your Views, Audios, Videos and more. Contact us: E-mail: info@habeshacults.com.


How Cults Work?

Cults, wonderful on the outside but on the inside are very manipulating. Cult leaders are desperate to trick you into joining!

Continue Reading »NewsLetter Sign Up !

Please enter your Email and Name to join.

Digital Newsletter

To unsubsribe please click here ».